12ኛው ዓለም አቀፍ የፖሊስ አካዳሚ ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ በህንድ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
12ኛው ዓለም አቀፍ የፖሊስ አካዳሚ ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ በህንድ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 13/2016 (ኢዜአ) ፦ 12ኛው ዓለም አቀፍ የፖሊስ አካዳሚ ህብረት ጠቅላላ ጉባኤ የፖሊስ አገልግሎት በቴክኖሎጂ ክስተትና በተፈጥሮ አደጋ ወቅት በሚል መሪ ቃል በህንድ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ የተመራ ልዑክ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
ህብረቱ እ.ኤ.አ 2011 የተመሠረተ ሲሆን የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ወቅታዊ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል የፖሊስ አባላት በማፍራት በጋራ መስራት ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።
ልዑኩ በ24ኛው የአስፈፃሚዎች ቦርድ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፍም ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከህብረቱ መስራች የፖሊስ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ጉባኤው በየዓመቱ ወቅታዊ በሆኑ የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና፣ እንዲሁም ምርምርና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት ሲሆን በዘንድሮው ጉባኤም ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ምላሽ የፖሊስ ሕጎች፣ የኮቪድ 19 ጉዳይ በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጻ የሚቀርብ መሆኑን ተመላክቷል፡፡