ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የኦዲት ሥርዓት ለመገንባት የዘርፉ ባለሙያዎች ሚና መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የኦዲት ሥርዓት ለመገንባት የዘርፉ ባለሙያዎች ሚና መጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/ 2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የኦዲት ሥርዓት ለመገንባት የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያበረክቱትን ሙያዊ አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።
በኢትዮጵያ የኦዲት ትግበራ ባህል የተመለከተ የግምገማ መድረክ የኦዲት ድርጅት አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታና የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚሁ ጊዜ፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የሒሳብና ኦዲት አገልግሎት ትልቅ ሚና አለው።
እንደ አገር ለውጥ ለማምጣት ከተጀመሩ ተግባራት መካከል የካፒታል ገበያ ማቋቋምና የውጭ ባንኮች እንደገቡ መፈቀዱን ጠቅሰዋል ከዚህ አኳያም ጥራት ያለው የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ጥራት ያለው ኦዲት ሥርዓት መዘርጋት ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተው የኦዲት ባለሙያዎች ዘመኑ የደረሰበት ጥራት ያለው የኦዲት ትግበራ ለማጠናከር በኃላፊነት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴክኒክና አቅም ግንባታ ሥራዎች በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።