ቡና የአርሶ አደሩን ሕይወት እንዲቀይር በቡና ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የዘርፉ ተዋንያን - ኢዜአ አማርኛ
ቡና የአርሶ አደሩን ሕይወት እንዲቀይር በቡና ገበያ መረጃ ስርዓት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የዘርፉ ተዋንያን
ዲላ ፤ህዳር 13/2016 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የቡና ገበያ የመረጃ ስርዓትን በመዘርጋት የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር እንደሚገባ የዘርፉ ተዋንያን ገለጹ፡፡
የዘርፉ ተዋንያን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቡና አለም አቀፍ የእርሻ ምርት በመሆኑ ተለዋዋጭ የገበያ ተጽእኖ በመቋቋም ግብይቱን ጤናማ ለማድረግ መረጃ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም ዓለም አቀፍ የቡና ገበያ መረጃን መሰረት ያደረገ የቡና ግብይት እንዲፈጠር በመስራት የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አቦሰ እንዳሉት ቡና ከሚያስገኝው የውጭ ምንዛሪ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ የማህበራዊ መስተጋብር መሰረት እንደሆነና ለአካባቢ ጥበቃ ድርሻው የጎላ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ቡና መገኛ ሀገርና እንደ ተፈጥሯዊ ጣዕም ባለቤት የተሻለ የፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፍ ያስፈልጋታል ያሉት ደግሞ ቡና ለሴቶች ጥምረት በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳራ ይርጋ ናቸው።
በተለይ ቡና የአምራች አርሶ አደሮችን ሕይወት ካልቀየረ የውጭ ምንዛሬ ማምጣቱ ብቻ ግብ ሊሆን አይገባም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ቡና ከምርት እስከ አቅርቦት ባለው ሂደት 70 በመቶ የሚሸፈነው በሴቶች ጉልበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በጥራት አጠባበቅና በግብይት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሴቶች አቅም ግንባታ ዙሪያ በስፋት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ዓለሙ ደሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ ስነ ምህዳሮች ተፈጥሯዊ ጣዕሙ ተመራጭና ተፈላጊ የሆነ ቡና አምራች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በተሳለጠ የገበያ ትስስር ውስንነት፣ የምርታማነት ችግርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ተፈላጊነት ልክ አምራች አርሶ አደሩንና ሀገርን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም ብለዋል፡፡
በተለይ ተለዋዋጭ የዓለም የቡና ገበያን ተረድቶና ተንትኖ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ የመለወጥ ክፍተት መኖሩን አመላክተዋል።
በዚህም የአምራች አርሶ አደሩ ሕይወት ሳይለወጥ መቆየቱን ጠቅሰው ይህን ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
የቡና ጥራት አጠባበቅና ግብይቱን በእውቀት እንዲመራ በተለይ መረጃን መሰረት ያደረገ ግብይት እንዲፈጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሰልጣን የምርት ጥራትና ሰርቲፊኬሽን የሀዋሳ ማዕከል ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሲማ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቡና በተፈጥሮ ባለው የጥራት አቅሙና ተፈላጊነቱ ልክ ከታች ጀምሮ የምርት ጥራት አጠባበቅ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
ቡና አለም አቀፍ የእርሻ ምርት በመሆኑ ተለዋዋጭ የገበያ ተጽእኖን በመቋቋም ግብይቱን ጤናማ ለማድረግ መረጃ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በምርት አሰባሰብ ወቅት የቡና ግብይትን ጤናማ ለማድረግ ህገወጥ ደላሎችን ከመቆጣጠርና ለተሻለ ጥራት የተሻለ ዋጋ ለመስጠት በየደረጃው እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይ ዓለም አቀፍ የእለት የገበያ ዋጋን ታሳቢ ያደረገ የሀገር ውስጥ የገበያ ስርዓትን ለመከተል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።