የራስ አገዝ ፕሮጀክት ለስኬት እንዳበቃቸው እናቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የራስ አገዝ ፕሮጀክት ለስኬት እንዳበቃቸው እናቶች ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/ 2016(ኢዜአ)፦ የራስ አገዝ ፕሮጀክት ለስኬት እንዳበቃቸው እናቶች ገለጹ።
በብዙ አገራት ሴቶችን ከድህነት በማውጣት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መካከል የሴቶች ራስ አገዝ ቡድን አሰራር አንዱ ነው፡፡
የፕሮጀክቱ ዓላማም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በፓለቲካና ማኅበራዊና ዘርፎች ለውጥ አምጥተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ነው።
የራስ አገዝ ቡድን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ሁሉን አቀፍ ለውጥ በማምጣት ከድህነት ለማውጣት አላማ በማድረግ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ሴቶች የሚያቋቁሙት ቡድን ነው።
በኢትዮጵያ በ20 ሴቶች በደብረ ብርሃን ከተማ በእየሩሳሌም ሕፃናትና ማኅበረሰብ ድርጅት አማካይነት ተጀምሮ ህዳር 2016 ዓ.ም 50ኛ አመቱ ላይ ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ 300 ሺ ሴቶች በ18 ሺ ቡድኖች በመደራጀትና ስልጠና በመውሰድ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን 320 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እናቶች በራስ አገዝ ቡድኖች የጀመሩት ትብብር ከድህነት አውጥቶናል ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል ወይዘሮ ትግስት እጅጉ፤ በሳምንት 50 ሳንቲም የሚያወጣ የቡና ፍሬ በመቆጠብ የጀመሩት ማህበር አሁን ላይ ከ2 ሺህ በላይ አባላትን በመያዝ ወደ ጥምረት ማደጉን ገልጸዋል።
በመሰረቱት ጥምረትም 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ካፒታል እና 16 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት የተሽከርካሪ ብድር መስጠት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በንግድ ሱቆች፣ በእንስሳት እርባታ፣ ትምህርት ቤት በመክፈትና በሌሎች ስራዎችም ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ከድህነት መውጣት ችለናል ነው ያሉት።
በርካታ እናቶች ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተነስተው በራስ አገዝ በትጋት ሰርተው ለስኬት መብቃታቸውን ወይዘሮ ትእግስት ገልጸዋል።
በአዳማ ከተማ የአብዲ ቦሩ የራስ አገዝ ቡድን አባል ወይዘሮ ነጻነት ሰርጸ፤ የራስ አገዝ ፕሮጀክት ከራስ አልፎ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር ያስቻለና ማህበረሰባዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን ያስረዳሉ።
በነገ ሰው ቡድን የድሬደዋ ጥምረት ስብሳቢ ወይዘሮ ሲሳይ መሸሻ፤ በሁለት ብር የጀመሩትን ቁጠባ 15 ብር በማድረስ የተሳካ ህይወት ለመምራት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
የራስ አገዝ ቡድን አሰራር ድርጅቶች ህብረት በኢትዮጵያ ተወካይ ዳይሬክተር ዳሬክ ይበልጣል፤ በኢትዮጵያ 33 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የራስ አገዝ ቡድኖችን አሰራር እየደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከእናቶቹ በተጨማሪም ወደ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ታዳጊዎች በቤተሰብ በሚመጣ ለውጥ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የራስ አገዝ ቡድን የሚያስተባብሩ ድርጅቶች ሥራቸውን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ለማቀናጀት ኅብረት ፈጥረዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድን አሠራር ድርጅቶች ኅብረት በኢትዮጵያ የሴቶችን አቅም በማጎልበት ላይ በሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተመሠረተ ሲሆን፣ በኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ኤጀንሲ በቁጥር 1591 ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል፡፡