በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው - የአፋርና አማራ ክልል ትምህርት ቢሮዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው - የአፋርና አማራ ክልል ትምህርት ቢሮዎች
አዳማ፤ ሕዳር 13/ 2016 (ኢዜአ)፡- ዘንድሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የቅድመ ዝግጅት ስራ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአፋርና አማራ ክልል ትምህርት ቢሮዎች ገለፀ ።
በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን እንደገለፁት ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 5ሺህ 300 የክልሉ ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት 19 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤት እጅጉን ዝቅተኛና ዓመታትን ያስቆጠረ የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይኸን ውጤት ለማሻሻል በክልሉ ያሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርትእየተሰጠ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የ'አፋር ታለንት አካዳሚ' ተቋቁሞ ወደ መማር ማስተማር ስራ ገብቷል ብለዋል።
አጠቃላይ የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻልም የትምህርት ግብዓት ማሟላት፣ የመምህራን አቅም ግንባታ፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና የክፍል ውስጥ የፈተና አሰጣጥ ስርዓት ማሻሻል ላይ ልዩ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
የ12ኛ ክፍል የመማሪያ መጻህፍትንም ለትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አቶ አብዱ አመልክተዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመደበኛና የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታማኝ አሸናፊ በበኩላቸው በክልሉ የ12ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል የትምህርት ጥራት ችግር የጎላ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''ውጤቱ ያሳየን የትምህርት ጥራቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ነው'' ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከመምህራን፣ ከርዕሰ መምህራን፣ ከተማሪ ወላጆችና ከተማሪዎች ጋር ሰፊ ወይይት መደረጉንና ከችግሩ ለመውጣት በአብሮነት መሰራት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
''ከትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ጀምሮ ሁሉም ያለበትን ሃላፊነት በየደረጃው እንዲወጣ አቅጣጫ አስቀምጠን በቅድመ ዝግጅት ላይ እየሰራን ነው'' ብለዋል።
ተማሪዎች እጅ ያልገቡ የመማሪያ መጻህፍት በ'ሶፍት ኮፒ' እንዲደርሱና ተማሪዎች በቡድን እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
በዘንድሮው ዓመት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲኖራቸው ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሃላፊዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በ2014 ዓ.ም ለፈተና ከቀረቡ ተማሪዎች 3 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ብቻ የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ሲሆን፤ በ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል ደግሞ 3 ነጥብ 2 በመቶዎቹ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣታቸው ይታወሳል።