የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌይ ውድድር ኅዳር 15 በመቀሌ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌይ ውድድር ኅዳር 15 በመቀሌ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦ 19ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌይ ውድድር ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም በመቀሌ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ ።
የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ እንግዳ፤ በውድድሩ ክለቦችንና ክልሎችን የሚወክሉ አትሌቶች የሚሳተፉበት መሆኑን ገልፀዋል።
በውድድሩ 6 አትሌቶች ከአንድ ክለብ ወይም ክልል የሚሳተፉበት የውድድር ዓይነት እንደሆነም ነው ያብራሩት።
በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ለሚወጡ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የ40 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ 20 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ለሚወጡት የ15 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የማራቶን ሪሌይ ውድድሩ ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም በመቀሌ የሚካሄድ ሲሆን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ 27ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም በዚያው የሚያካሂድ ይሆናል።
በ2015 ዓ.ም በተካሄደው 18ኛው የኢትዮጵያ የማራቶን ሪሌይ ውድድርና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በሰመራ መካሄዱ ይታወሳል።