ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነት ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላት ሰፊ ዝግጅት መደረግ አለበት- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነት ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላት ሰፊ ዝግጅት መደረግ አለበት- ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነት ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላት ሰፊ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ተጠቃሚነት ጥያቄ፣ ከብሪክስ አባልነት ጉዳዮችና የሠላም ስምምነቶች ባመጡት ውጤቶችና ሌሎችም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው ላነሳቸው ጥያቄዎች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገኦ፤ ኢትዮጵያ በብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
በመስኩ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁመው፤ በዚህ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነቷ ማትረፍ እንድትችል የሚያደርግ በቂ የሰው ኃይል አለ ወይ? በቂ ጥናትና ምርምሮች እየተደረጉ ነው ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ሊታዩ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አኳያም የውጭ ባለኃብቶች ወደ አገር ውስጥ በብዛት እንዲመጡና መዋዕለ- ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።
በሕገ-ወጥ መንገድ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሕጋዊ መስመር ገብተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ላይም ሚኒስቴሩ መፍትሔ ተኮር ሥራዎችን ማከናወን አለበት ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገቻቸው የሠላም ስምምነቶች ከአገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት አሻሽሎታል ብለዋል።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ሕብረትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ግንኙነቱ መጠናከሩን ተናግረዋል።
ከቀይ ባህር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄም "ቀይ ባህር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ይያያዛል" በማለት አብራርተዋል።
" የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጠቃሚነት ጥያቄ ፍትሃዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ ነው፤ ይህም በሌሎች አገራት ላይ ስጋትን የሚፈጥር ሊሆን አይገባም " ሲሉ ተናግረዋል።
በቀይ ባህር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለአገራት የማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በንግድ ልውውጥና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው ብለዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ከዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ ሲያብራሩ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥረቱን ቀጥሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያን አባል ለማድረግ የተጀመረው ድርድር አራተኛው ዙር መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ወደ አምስተኛው ዙር ድርድር ለመሸጋገር ሂደቶች ተጀምረዋል ሲሉ ተናግረዋል።