አመራሩ በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋዎች በአግባቡ ተረድቶ በመስራት የተጀመረውን የለውጥ ሂደቱን በውጤት ማስቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋዎች በአግባቡ ተረድቶ በመስራት የተጀመረውን የለውጥ ሂደቱን በውጤት ማስቀጠል አለበት
ዲላ ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦ አመራሩ በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋዎች በአግባቡ ተረድቶ በመስራት የተጀመረውን የለውጥ ሂደቱን ውጤት ማስቀጠል እንዳለበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሊድ አልዋን ገለጹ።
በዲላ ማዕከል ሲሰጥ የቆየው የ3ኛ ዙር የመንግስት አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና የአቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታ በማስጀመር ተጠናቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሊድ አልዋን በማጠቃለያው መርሃ ግብር ላይ እንዳሉት፤ ስልጠናው ህብረብሔራዊ አንድነት የተንጸባረቀበትና ኢትዮጵያዊነት ጎሎቶ የታየበት ነው።
በተለይ የንድፈ ሃሳብ ስልጠናን ከአካባቢው ተሞክሮ ጋር በማቆራኝት የተሻለ ልምድና አቅም ከመፍጠር ባለፈ በጌዴኦ ዞን የለውጡ ትሩፋት የሆኑ የልማት ስራዎችን መጎብኝት መቻሉን አስረድተዋል።
ሰውና ተፈጥሮ ተስማምቶ መኖር እንደሚችል ከጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ልምድ መወሰዱን ጠቅሰው ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህም መንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ ለመውጣት የሚያስችል የአመራር ቁመና መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ ኢትዮጵያን ከእዳ ወደ ምንዳ ለማሸጋገር መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በተለይ አመራሩ በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋዎች በአግባቡ ተረድቶ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በውጤት ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ዓመራሩ ከስልጠናው ጎን ለጎን ከ560 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት በጌዴኦ ዞን የአራት አቅመ ደካማ ወገኖች የቤት ግንባታ ማስጀመር መቻሉን ጠቅሰዋል።
ከሰልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማረቆ ልዩ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሻለ ገትሶ በበኩላቸው የተሳሳቱ ትርክቶችና አካባቢያዊነት የኢትዮጵያ እዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም ህብረ ብሔራዊነትን ለማጽናት ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ የአመራሩ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው አብሮነትን በማጠናከር ለእድገት ለመትጋት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች መካከል አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ በበኩላቸው ስልጠናው በአካባቢያችን ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ትልቅ ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም በማስፈንና የኑሮ ውድነት ችግርን ለማስወገድ ህብረተሰቡን በማስተባበር በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ ካላቸው ጥቂት ጥሪት በማዋጣት በጎ ተግባራትን ማከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል።