በባሌ እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
ሮቤ/ነገሌ ቦረና ፤ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦በባሌ እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
በባሌ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በቦንድ ግዥው ከተሳተፉት መካከል የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሠራተኞች መካከል አቶ ድሪባ ገላልቻ በሰጡት አስተያየት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ በአገሪቱ ዜጎች ላብ የሚገነባ የአንድነት ዓርማ ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ለ5ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ጠቅሰው፣ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።
''የግድቡ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁ በግድቡ ላይ የነበረኝ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲነሳሳ አድርጎኛል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የጽህፈት ቤቱ ሠራተኛ አቶ ሸዋቀና ከበደ ናቸው።
የዘንድሮ ሙሌት የግድቡን የግንባታ ሂደት እውን ማድረግ እንደምንችል በተግባር ያሳየን በመሆኑም "የጀመርኩትን ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክሬ እቀጥልበታለሁ" ነው ያሉት።
የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልቺሳ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የሴክተሩ ሰራተኞች ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ለግድቡ ግንባታ በአንድ ቀን የፈጸሙት ከ55 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዥና ስጦታ በምሳሌነት የሚጠቀስና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው።
የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ በበኩላቸው፣ በዞኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ውጤታማነት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 28 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥና ስጦታ ለማሰባሰብ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
እስከ አሁን በተደረገው ጥረትም ከ17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና ስጦታ ለማሳበሰብ መቻሉን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ህብረተሰቡን ለድጋፍና ትብብር ያነሳሳ መሆኑን የምስራቅ ቦረና ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡
ከዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉም ተገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊና የግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ መሳይ ጥላሁን በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ገቢ የመሰብሰብ ስራው በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል።
በበጀት አመቱ ብቻ ከዞኑ በስጦታና በቦንድ ግዥ መልክ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በስጦታ፤ 9 ሚሊዮን 848 ሺህ 749 ብር ደግሞ በቦንድ ግዥ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ምስራቅ ቦረና በዞን ደረጃ እንደ አዲስ ከተቋቋመ ወዲህ የዞኑ ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 16 ሚሊዮን 667 ሺህ 942 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ጥቅም እስኪቀየር ድረስ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።
በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ መደረጉን ከዞኑ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፋት ቤት የተገኛው መረጃ ያመለክታል።