የአማራ ክልል ህዝብን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ህዝብን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፣ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ) ፦ የአማራ ክልል ህዝብን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ የ3ኛው ዙር የመንግስት አመራር አባላት የስልጠና ተሳታፊዎች የማጠቃለያ ፕሮግራም ትናንት ምሽት ተካሂዷል።
ርእሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው።
የክልሉን ህዝብ በሁለንተናዊ ልማትና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥም እየተሰራ ነው ብለዋል።
''ሰላምና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት ከቻልን የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የሚረጋገጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም'' ሲሉም ገልጸዋል።
ስልጠና ላይ የቆዩ ሰልጣኝ አመራሮች የተያዘውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
''የተሰጠው ስልጠና ዋና አላማም የትናንትና የዛሬ ችግሮቻችንን በመፍታት ወደ ብልፅግና ጉዞ የምንገሰግስበትን ጠንካራ አቅም ለመገንባት ያለመ መሆኑን'' ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በምክትል ርእስ መስተዳድር ማእረግ የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት ዋና አማካሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ የስልጠናው ተሳታፊዎች ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ ለህዝቦች አንድነትና ትስስር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ሰልጣኞች ከስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን አቅም ወደ መልካም እድል በመቀየር ለለውጥ መትጋት እንዳለባቸውም አክለዋል።
በባህር ዳር የስልጠና ማዕከል ለ12 ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲሰጥ የቆየው የመንግስት የአመራሮች ስልጠና ትናንት ምሽት ተጠናቋል።