ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በወራቶች ውስጥ በስድስት የተለያዩ አገራት ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎች ይኖሩታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በወራቶች ውስጥ በስድስት የተለያዩ አገራት ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎች የሚኖሩት መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ ለማ ያዴቻ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አየር መንገዱ አውሮፕላኖችን በመግዛትና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎቹን በፍጥነት እያሳደገ መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሁን ላይ 136 መድረሱን ጠቅሰው በወራቶች ውስጥ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎች ይኖሩታል ብለዋል።


 

ከቀናት በኋላ ወደ ስፔን ማድሪድ በረራ የሚጀምር መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው በጥቂት ወራቶች ውስጥ ሌሎች ተጨማሪ መዳረሻዎች ይኖሩታል ብለዋል። 

በዚህም አየር መንገዱ ወደ ሴራሊዮን ፍሪታውን፣ አውስትራሊያ፣ ቬትናም ሃኖይ፣ ሆላንድ አምስተርዳም እና ሰሜን አፍሪካ በረራ የመጀመር ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ጉብኝት አየር መንገዱ ወደ ደብሊን መብረር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመነጋገር መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ጥቂት ቀናት ወደ መካከለኛው አፍሪካ ባንጉይ እንዲሁም ከትናንት በስቲያ  ወደ እንግሊዝ ለንደን ጋትዊክ አዲስ በረራ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ከቦይንግና ኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያዎች በድምሩ 84 የመንገደኞች አውሮፕላን ለመግዛት ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም