ቀጥታ፡

ባለፉት ሶስት ወራት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፦ባለፉት ሶስት ወራት በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን  የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የተቋሙን የ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም በሚመለከት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ርዳታና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም በሰባት ክልሎች በድርቅና የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ 500 ሺህ ዜጎች በአፋጣኝ ድጋፍ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህል ተደራሽ መደረጉን ነው የጠቀሱት።

ከዚህም ባሻገር ከዓለም ባንክ የተገኘ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ በልማታዊ ሴፍቲኔት ማዕቀፍ ለሌሎች ተፈናቃይ ዜጎች መሰራጨቱን ጠቅሰዋል። 

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ በሁለት ዙሮች በተከናወኑ የድጋፍ መርሃ ግብሮች ለ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ድጋፍ ፈላጊ ወገኖች የሰብዓዊ ርዳታና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ኮሚሽነሩ ገለጸዋል።።

በተጨማሪም በቅርቡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አቋርጦት የቆየውን ድጋፍ ለመጀመር ፍላጎት ማሳየቱ መንግስት እያቀረበ ላለው ድጋፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በመሆኑም ድርጅቱ የሚያከናውነውን ድጋፍ በኮሚሽኑ በኩል ተደራሽ ለማድረግ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን አክለዋል።  

በዋናነትም መንግስት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ከማቅረብ በዘለለ የራስ አቅምን ማጠናከር ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ቅነሳዎች ላይ በጥናት የተደገፉ ስራዎችን ማከናወንና ለዚህ ዝግጁ የሆነ አመራር መፍጠር ዓቢይ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም  በብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት አማካኝነት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ለአብነትም በማህበረሰቡ ዘንድ የተረጂነት አመለካከትን ማስወገድ፣ ችግር በሚያጋጥም ጊዜ በራስ አቅም ምላሽ የሚሰጥ የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም