በ28ኛው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኢትዮጵያ የራሷን ተሞክሮዎች ታካፍላለች - ኢዜአ አማርኛ
በ28ኛው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኢትዮጵያ የራሷን ተሞክሮዎች ታካፍላለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2016(ኢዜአ)፦በዱባይ በሚካሄደው 28ኛው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኢትዮጵያ የራሷን ተሞክሮዎች እንደምታካፍል የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ከተማ የሚካሄደውን ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ጉባዔው በየዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚሁ የሚሆኑ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውም ተመላክቷል።
ጉባዔው ከኅዳር 20 እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድና ከ130 በላይ አገራት በመሪዎች ደረጃ እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል።
በጉባዔው በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች እንደሚደረጉ፣ አገራት አቋማቸውን እንደሚያሳውቁ እንዲሁም በሁለትዮሽ መድረኮች በርካታ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።
የድርድር መድረኮችም ሌላኛው የጉባዔው አካል መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ትልቁን ቦታ የሚይዝ መሆኑን አመላክተዋል።
የፓሪሱ ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ የጉባዔው ትልቅ አጀንዳ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለውሳኔ ሰጪዎች መነሻ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 ስምምነት የተደረሰበትን የፓሪሱን አጀንዳ ተፈጻሚ ከማድረግ አኳያ አገራት ምን አከናወኑ? የሚለው በዚሁ መድረክ የሚዳሰስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከመደበኛው ውይይቶች ባሻገር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ የራሷን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እንዲሁም በተጨባጭ መሬት ላይ እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎችን የምታሳይበት መሆኑን አብራርተዋል።
በጉባዔው በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን እና ከዚህ ቀደም ከነበሩት መድረኮች በተለየ ትልቅ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።
ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የዓለምን የሙቀት መጠን ለመቀነስ ምክክር የሚደረግበት ነው።
ጉባዔው መካሄድ ከጀመረ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች መጨመር ለጉባዔው መጀመር ዋንኛው ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።