በዞኖቹ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው

ግምቢ፤  ህዳር 12/2016 (ኢዜአ)፡- በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የመጣው ውጤት ለችግኝ እንክብካቤ እንዳነሳሳቸው የዞኖቹ ነዋሪዎች ገለጹ።

በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ባሉ ወረዳዎች ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተተከሉ ችግኞች የጥበቃና የእንክብካቤ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን በችግኝ እንክብካቤው ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የዩብዶ ወረዳ ነዋሪው አቶ ደገፋ ሰንበቶ እንዳሉት በወረዳቸው በየዓመቱ ሀገር በቀል ችግኞች ሲተከሉ ቆይተዋል።

የተተከሉ ችግኞች ለታለሙለት ዓላማ እንዲደርሱም "በተከላው መርሃ ግብር እንደተሳተፍን ሁሉ በእንክብካቤውና በጥበቃው ስራ ላይም በመሳተፍ ላይ እንገኛለን" ብለዋል፡፡

"ባለፉት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች የተገኙት ጠቀሜታዎች ለወደፊቱ የበለጠ እንድንተክልና እንድንካባከብ መነሳሳት ፈጥሮልናል" ሲሉም አክለዋል።

"ችግኝ መትክል ብቻ ግብ አይደለም" ያሉት ደግሞ በዞኑ የነጆ ወረዳ ነዋሪ አቶ ይፍሩ ዳቃ ናቸው፡፡ 

"ተፈጥሮ እንክብካቤ ይወዳል" ያሉት ነዋሪው፤ ''ባለፉት ዓመታት የሰራናቸው ስራዎች ውጤቱ አስደሳች መሆኑን ተገንዝበናል አጠናክረን እናስቀጥላለን'' ሲሉም ተናግረዋል።

''በአካባቢያቸው በተተከሉ ችግኞች የደን ሽፋን ጨምሯል፣ የአፈር መራቆትም ቀንሷል'' ያሉት ደግሞ የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ያዳታ ሽብሩ ናቸው።

በዚህም በመነሳሳት ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባክብ ከሌሎቹ ነዋሪዎች ጋር በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፋይሳ ሃምቢሳ በበኩላቸው ባለፈው ክረምት በዞናቸው ከ250 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተተክለዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል 90 በመቶ የሚጠጋ ችግኝ መጽደቁን በባለሙያ በተደረገ ዳሰሳ ለማየት መቻሉንም አክለዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ ለተተከሉት ችግኞች እየተደረገ ካለው እንክብካቤ ጎን ለጎን ለቀጣዩ የችግኝ ተከላ ስራ የችግኝ ጣቢያዎችን የማዘጋጀትና የዞኑን አርሶ አደሮች በብዛት የማሳተፍ አቅጣጫ ተይዞ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን ባለፈው ክረምት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለተተከሉ ችግኞች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የችግኝ ጥበቃና የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ ነው።

አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ተማሪዎች  ደግሞ በእንክብካቤ ስራው ላይ ተሳታፊ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል መሆናቸው ታውቋል።

የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው የአካባቢን ልምላሜ ሲለውጡ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም የሚሉት ተሳታፊዎቹ፤ ይህም የበለጠ ለመትከልና የተተከሉትን ለመንከባከብ የሚያነሳሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙለታ ዋቅጂራ በበኩላቸው በዞኑ ባለፈው ክረምት ከ42 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በ15 ሺህ 124 ሔክታር መሬት ላይ መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተተከሉት መካከል  ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም  በዞኑ በ12ቱም ወረዳዎች በህብረተሰቡ ተሳተፎ የጥበቃና የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን በዘመቻ መልክ የመንከባከብ ስራ ከትናንት ህዳር 11  ጀምሮ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም