ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ዲጂታል የማሸጋገር ስራ እየተሰራ ነው - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ከተሞችን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ዲጂታል የማሸጋገር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡  

የመንግሥት የ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተጀምሯል። 

በግምግማው የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የስራ እንቅስቃሴዎች ተዳሰዋል፡፡ 

የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ለማዘመን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡   

በስድስት ከተሞች የአገልግሎት ደረጃዎችን በማዘጋጀት  ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከተሞቹ በቄራ አገልግሎት፣ በአረንጓዴ ልማትና የከተማ ውበት፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ  እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እና ከሰው ንክኪ ነጻ  ወደ ሆነ ዲጂታላይዜሽን ለማሸጋገርም ለአብነት በቀብሪደሃር፣ ጅግጅጋ፣ በደብረብርሃን እና ቢሾፍቱ ከተሞች ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በእነዚህ ከተሞች የሚገኘውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት ዕቅድ መያዙንም ጠቅሰዋል።

የከተሞች የመሬት አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን በካዳስተር ስርዓት መመዝገብ መጀመሩን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ይህም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እና ብልሹ አሰራሮችን ለመቅርፍ ያስችላል ብለዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከከተሞች የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

የከተሞች የገቢ አቅም ማደጉ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር፣ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እና መሰረተ ልማቶችን በራስ አቅም ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም