በሩብ ዓመቱ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ ዓመቱ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ) ፦በሩብ ዓመቱ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውሃና ኢነርጂሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ቴክኖሎጂ የማላመድና "የግድቤን በደጄ" ስራዎች በቀጣይ በትኩረት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሚኒስቴሮች የስራ አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ የውሃ ሃብት አስተዳደርና የኢነርጂ ልማት ስራ አፈጻጸም ተገምግሟል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ የሚኒስቴሩ አጠቃላይ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ከ90 በመቶ በላይ ተሳክቷል ብለዋል።
በሩብ ዓመቱ በተለይ የንጹህ የመጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ ሰፊ ሰራዎች ተሰርተው ጥሩ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ በማድረግ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኤሌክትሪክን ከዋናው መስመር በመሳብ 100 ሺህ አባወራዎች ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ከዋናው የሃይል መስመር ውጭ ከጸሃይ ብርሃንና ከሌሎች የሃይል አማራጮች በርካታ የገጠር ከተሞችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን በመጥቀስ በዚህ ተግባር 2 ሺህ አባዎራዎች የኤሌክተሪክ ኃይል አግኝተዋል ብለዋል፡፡
በውኃ አስተዳደር ዘርፍ ተፋሰሶችን በመለየትና የውሃ ሃብት መለኪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መረጃ የመሰበሰብ ተግባር ማከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሩብ አመቱ የኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ ዳዋ እና ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች መሪ እቅድ የወጣላቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሌሎችም ተፋሰሶች ይቀጥላል ብለዋል።
በድርቅ በተደጋጋሚ በሚጠቁ አካባቢዎች ቴክኖሎጂን የማላመድና ግድቤን በደጄ መርህ የዝናብ ውሃን በመያዝ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።