ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል የኪነ-ጥበብ ምሽቶችን ዳግም ማዘጋጀት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 12/2016 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል የኪነ-ጥበብ ምሽቶችን ዳግም ማዘጋጀት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር  ጥምረት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ የባህል ማእከሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪና የማይረሱ ስራዎችን በማከናወን አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የባህልና የቋንቋ ፖሊሲ ከመረቀቁ በፊት፣ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ባልተስፋፉበት ጊዜ የባህል ማዕከል ለግማሽ ክፍለ ዘመን በሰራቸው ድንቅ የኪነ ጥበብ ስራዎች የማይደበዝዙ አሻራዎችን ያኖረ መሆኑን አስታውሰዋል። 

በመሆኑም የማዕከሉን የኪነ-ጥበብ ምሽቶች እንደገና ማስጀመር አሁንም ለዘርፉ እድገት ትልቅ ትርጉም የሚኖረው መሆኑን ገልጸዋል።

ከትምህርታቸው ባሻገር ሁለንተናዊ የስብዕና መገንቢያና የተሻለ የትምህርትና የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ባህል ማዕከሉን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ፤ የባህል ማዕከሉ በሀገሪቷ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት ባለውለታ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዘርፉ እድገት አሁንም የራሱን አሻራ በማኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ ዘወትር ማክሰኞ የኪነ-ጥበብ ምሽት ዳግም ማዘጋጀት ይጀምራል ብለዋል።

በየሳምንቱ ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ ደግሞ ፊልም የሚያሳይ ሲሆን በቀረቡት ፊልሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ የፊልም የውይይት መድረክ የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር  ጥምረት ጋር በመተባበርም ለባህል ማዕከሉ ዕድገት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውን መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ፕሬዘዳንት ተክሉ አሻግር፤ የኢትዮጵያን ሰርከስ ለማሳደግና ኢትዮጵያን የሰርከስ ማዕከል ለማድረግ ከባህል ማዕከሉ ጋር  መሥራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰርከስ በዓለም ላይ የታወቀ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ለዘርፉ እድገት አጋዥ የሆኑ ስራዎችን ለመስራት በ11 ነጥቦች ላይ የሚያተኩር የመግባቢያ ስምምነት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ዋነኛ ዓላማም የሰርከስ ጥበብ ፖሊሲ ለማርቀቅና ለማፀደቅ፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በሰርከስ ዙሪያ ለማከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የሰርከስ ታሪክ ጥናት በማድረግ አሳትሞ ለማሰራጨት እንዲሁም በአፍሪካ መሪ የሆነ የሰርከስ የኪነ-ጥበብ ማዕከል ግንባታ ለማከናወን ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። 

በ1956 ዓ.ም የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የባህል ማዕከል የመጀመሪያ የኪነ-ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም