አፍሪካ ከአጋር አከላት ጋር በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት ለመስራት ዝግጁ ናት - ሙሳፋቂ መሃመት 

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ በሁሉም ዘርፍ ካሉ አጋር አከላት ጋር በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት ለመስራት ዝግጁ ናት ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳፋቂ መሃመት ተናገሩ።

በጀርመን በርሊን በተካሄደው የ'ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ' ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳፋቂ መሃመት አፍሪካ የጋራ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ተግባራት በሯ ክፍት ነው ብለዋል።

በአህጉሪቷ ያለውን የኢንቨስትመንት ሀብት በሁለትዮሽ ትብብር በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን ሲሉም ነው ያረጋገጡት።

የአፍሪካ ሀገራት እንደ ጀርመንና ቻይና ካሉ ሀገራት ጋር ሚዛኑን በጠበቀ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት እየሰሩ መሆኑንም አውስተው ''ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ' ጉባኤም በዚህ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

እንደ አህጉር በኢንቨስትመንት መዳረሻዎችና በሌሎች መስኮች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም አጋር አካላት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ማመልከታቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።

በ2017 የጀርመን የጂ20 ፕሬዝዳንትነት ዘመን የተጀመረው የጂ20 'ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ' ጉባኤ ለውጥ ተኮር በሆኑ የአፍሪካ ሀገራት፣ በጂ 20 አጋሮች ብሎም ከእነዚህ ባሻገር ባሉ አካላት መካከል የንግግር እና የትብብር መድረክ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም