ቀጥታ፡

አካታችና አሳታፊ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የተጀመሩ ተግባራት መጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 11/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት ለማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምጽ እንዲሰማ የሚያከናውናቸው ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላከተ።   

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር አገራዊ ምክክርን አስመልክተው ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ምክር ቤት የፕሮግራምና ልማት ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል በዚሁ ጊዜ፤ ምክር ቤቱ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ለምክክሩ ስኬት ምቹ ምህዳር ለመፍጠርና ማኅበረሰቡ በምክክሩ በነቂስ እንዲሳተፍ በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ለሕዝቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የፕላንና ልማት አማካሪ  ሞገስ ደምሴ፤ አካታችነት ማረጋገጥ የአገራዊ ምክክር ዋነኛው ተግባር ነው ብለዋል። 

በዚህ ረገድ የሲቪል ማኅበራት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አካታች የምክክር ሂደት እንዲካሄድ አመርቂ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል ፍሬው ተስፋዬና ተስፋ አወቀ፤ ኮሚሽኑ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት። 


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ የሁሉም ዜጎች ኃሳብ የሚንጸባረቁበት እንዲሆን እየተሰራ ነው። 

በውይይቱ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የምክክሩን ሂደት ስኬታማ ማድረግ የሚችሉ ተግባራትን በማከናውን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።    

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ሰላም የሆነችና ለዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን መገንባት ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ለዚህም እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።  

የኢትዮጵያን ሥር የሰደዱ ችግሮች በምክክር በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ድርሻ ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1265/ 2014 ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ማፅደቁ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም