ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ኮሌራ፣ ወባና ኩፍኝ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባህር ዳር፣፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ኮሌራ፣ ወባና ኩፍኝ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

በክልሉ የኮሌራ፣ ወባና የኩፍኝ በሽታዎችን የስርጭት ደረጃ የሚገመገም የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል በተለይም በኮሌራ፣ በወባ እና በኩፍኝ በሽታዎች ምክንያት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመለካለል ስራው በጋራ እየተከናወነ ነው።

በሽታዎችን ለመከላከል ተገቢውን ግብአት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ባለሙያ በመመደብ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው ውይይትም በሽታዎቹ ያሉበት ደረጃ በመለየት የተጀመሩ ድጋፎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሆነም አብራርተዋል።

የአማራ የክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ በሽታ ለመቆጣጠር የቅንጅት ስራዎች ከላይ እስከታች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በጎንደርና በጎጃም አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን የኮሌራ በሽታ በተደረገ የተቀናጀ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉንም አብራርተዋል።

አሁን ላይ ደግሞ በሰሜን ወሎና ዋግምኸራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሽታው መከሰቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በቁጥጥር ስር ለማዋል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዛሬው ውይይት አላማም በክልሉ በወረርሽኝ መልክ እየተከሰቱ ያሉ በሽታዎችን በጥልቀት በመገምገም በቀጣይ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት ነው ብለዋል።

በክልሉ አራት ሽህ 800 በላይ ሰዎች በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሲሆን በተደረገላቸው ህክምና ጤንነታቸውን መመለስ እንደተቻለ ተገልጿል።

በዚሁ የውይይት መድረክ የፌዴራልና የክልል የህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም