ቀጥታ፡

በኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን መለየትና መፍትሄ መስጠት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፍ ያልተዘረጋላቸው አሰራሮችን በመፈተሽ የማሻሻያ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ  እንደሚገባ ተመላከተ።  

የአዲስ አበባ የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን በኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ያለውን የሙስና ተጋላጭነትን በሚመለከት ባካሄደው ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ቡድን መሪ ጥላሁን ብርሃኔ የጥናቱን ይዘት በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።

ጥናቱ ከማዕከል እስከ ወረዳ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ሴክተሮችን ጨምሮ በሥራቸው ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል። 

የተቋሙን አሰራር መዳሰስ፣ የሙስና ተጋላጭነትና መንስዔዎችን መለየትና ተጠያቂነትን ማስፈን የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት፤ ኤጀንሲው ኃብትና ንብረትን በአግባቡ ማስተዳደርና በከተማ አስተዳደሩ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሰጠው የተዘዋዋሪ ብድር አሰጣጥን በሚመለከት የአሰራር ሥርዓት ክፍተት እንዳለበት ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል።

ገቢና ወጪዎችን በተገቢው መልኩ ኦዲት ማስደረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ አለማድረግ፣ ለዘርፉ የሚመጥኑ ሙያተኞችን ማብቃት ላይም እንዲሁ በቂ ሥራዎች አለመከናወናቸው ተመላክቷል። 

በመሆኑም ኤጀንሲው በኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመለየት  የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። 

በዋናነትም በኅብረት ሥራ ማኅበራት የሕግ ማዕቀፍ ያልተዘረጋላቸው አሰራሮችን በመፈተሽ የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወንና የሙስና ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ ምክረ ኃሳብ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው ጥናቱ የተቋሙ አሰራር ለሙስና ተጋላጭ እንዳይሆን እየተከናወነ ያለውን የሪፎርም ሥራ የሚደግፍ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የጥናቱን ምክረ ኃሳቦች በአግባቡ ገቢራዊ በማድረግ ተቋሙ ለሙስና ታጋላጭ እንዳይሆን በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።  

የአዲስ አበባ የሥነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በጥናቱ የቀረበው ምክረ-ኃሳብ ተፈጻሚ እንዲሆን አስፈላጊው እገዛና ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም