ቀጥታ፡

የግብርና ምርቶችን የወጭ ንግድ ለማሳደግ የገበያ አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦የግብርና ምርቶችን የወጭ ንግድ ለማሳደግ እሴት መጨመር ማቅረብና የገበያ አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ።

የተለያዩ አገራት ተወካዮች የተሳተፉበት 12ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጉባዔው ከ400 በላይ የአገር ውስጥ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብአትና ማሽነሪ አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎችና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ስራ አመራር ቦርድ ሊቀመንበር ሲሳይ አስማረ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ እሴት ጨምሮ በመላክ ረገድ ብዙ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።


 

በተለይም የቅባት እህሎች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም ከሚፈለገው ውጤት አኳያ አጥጋቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

አርሶ አደሩን ከባለሃብቱ ጋር በማገናኘት የተሻለ ምርትና ምርታማነት እንዲኖር የማድረግና እሴት በመጨመር ዙሪያ ማህበሩ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ የግብርና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት ይገባል ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው የግብርና ምርቶች መካከል የጥራጥሬና ቅመማ ቅመም ምርት ዋነኛው በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። 


 

ለግብርና ምርቶቹ ያለውን ምቹ ስነ-ምዕዳር በመጠቀም በጥራትና በብዛት በማምረት የውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ድርሻ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የጉባኤው መካሄድ ዓለም አቀፍ ገዥዎችን፣ ላኪዎችን፣ የእርሻ ምርት ግብአት አቅራቢዎችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትና አገልግሎት ሰጪዎችን በማገናኘት ጠንካራ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑ ተነስቷል።

የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ላስገኙ ላኪዎች በጉባኤው ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጉባኤው መዘጋጀቱ ታውቋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም