ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የግል ድርጅት ሠራተኞችን አስተዳደራዊ በደል የማየት ሥልጣን ተሰጠው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የማሻሻያ አዋጅ የግል ድርጅት ሠራተኞችን አስተዳደራዊ በደል የማየት ሥልጣን የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን የማሻሻያ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።  

የምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ የተቋሙን የማሻሻያ አዋጅ ዝርዝር ሁኔታና አስፈላጊነቱን በሚመለከት ለምክር ቤቱ አባላት በዝርዝር አቅርበዋል።

የተደረገው ማሻሻያ የአስተዳደር በደሎችን ለመከላከል እና ተፈጽሞ ሲገኝ ምርመራ በማካሄድ በደሎች በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ቀርቶ በዕንባ ጠባቂ ጉባዔ የሚመደብ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተቋሙ መርማሪ በምርመራ ሥራ ላይ እያለ ዋና ዕንባ ጠባቂ ሳይፈቅድ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር አይያዝም፤ አይከሰስም፤ እንዲሁም ያለመታሰር መብት እንዳለው በአዋጁ መደንገጉንም ገልፀዋል።

በተደረገው ማሻሻያ መሠረትም በመርማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ያልተገባ ጫና በማስቀረት ነፃነታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግል ድርጅቶች የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችን የማየት ሥልጣን እንዳልነበረው አስታውሰው፤ በተሻሻለው አዋጅ ግን የማየት ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን የመቀበል፣ የመመርመር እና ምክረ-ሃሳብ የማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑንም አስረድተዋል።

በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአዋጁን ማሻሻያ ተገቢነት በማመን በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ አዋጅ ቁጥር 1142/2011 በአዋጅ ቁጥር 1307/2016 ተሻሽሎ በምክር ቤቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ  ደንብ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

የጋዜጠኝነት ሥራ በባህሪው በየትኛውም ሰዓት ሥራ ላይ መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ እነሱን የሚመለከት ድንጋጌ ባካተተ መልኩ መሻሻሉ አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል። 

ኢቢሲ ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ይዞ ለማቆየት እና አዳዲስ ልዩ ችሎታና ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞች ለመቅጠር እንዲችል ደንቡን ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።

በዚህም መሠረት የኢቢሲ የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብን ደንብ ቁጥር 1/2016 ሆኖ በምክር ቤቱ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም