ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ መሰረተ ልማቶችን በማዘመን ወደ ስማርት የከተማ ሥርአት ለማስገባት ይሰራል---አስተዳደሩ

ባህር ዳር፣ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ በተያዘው ዓመት መሰረተ ልማቶችን በማዘመን ወደ ስማርት የከተማ ሥርዓት ለማስገባት እንደሚሰራ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።

ምክትል ከንቲባው አቶ አስሜ ብርሌ እንደገለጹት የባህር ዳር ከተማን ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ለማድረግ እየተሰራ ነው። 

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የአስፋልት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የጌጠኛ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

ዘንድሮም የልማት ሥራዎችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ቀደመው የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ለማዘመን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም በዋና ዋና የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ በመግጠም የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማቀላጠፍና የፀጥታ ሥራውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚሰራውን ሥራ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

በቴክኖሎጂ የሚደገፉ ሥራዎች ከተማዋን ወደስማርት ከተማነት ለማሸጋገር የተያዘውን ግብ ለማፋጠን የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል።

አቶ አስሜ እንዳሉት፣ በከተማዋ በቅርቡ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ከከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር በተሰራ ሥራ በአሁኑ ወቅት ሰላም ሊሰፍን ችሏል።

በቀጣይም በሁሉም ቀጣናዎች የሰላም ኮሚቴ በማዋቀር የከተማዋን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። 

"ባህር ዳር በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ እንቅስቀሴ የሰፈነባትና ሰፋፊ የልማት ሥራዎች የሚከናወኑባት ሞዴል ከተማ ናት" ያሉት ደግሞ በከተማዋ "ከእዳ ወደ ምንዳ" በሚል እየተሰጠ ባለ የአመራር ስልጠና የተሳተፉት አቶ ፍቃዱ ኦሳይ ናቸው።


 

ከተማዋ በትላልቅ የአስፋልት መንገዶች፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሻለች በመሆኗ ለቱሪዝም ተመራጭ ከተማ መሆኗን ጠቅሰዋል። 

"በከተማዋ ባየሁት ለውጥ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ልማትን ለማፋጠን ተስፋ እንዳለ ተገንዝቤያለሁ" ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ ከስልጠና በኋላ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ሊተገበር የሚችል ተሞክሮ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ በተያዘው ዓመት ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መድቦ ወደ ተግባራዊ ሥራ መገባቱ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም