በምስራቅ ቦረና ዞንና ነቀምቴ ከተማ የችግኝ እንክብካቤ ስራ በመከናወን ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞንና ነቀምቴ ከተማ የችግኝ እንክብካቤ ስራ በመከናወን ላይ ነው

ነገሌ ቦረና/ነቀምቴ ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦ የተተከሉት ችግኞች አድገው የድርቅ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባለፈ ለታለመለት ግብ እንዲደርሱ የእንክብካቤ ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የምስራቅ ቦረና ዞንና ነቀምቴ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ።
በምስራቅ ቦረና ዞን የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ለታለሙለት ግብ እንዲደርሱ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የአረንጓዴ ልማት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ በመከናወን ላይ ነው።
በእንክብካቤ ስራው ላይ በመሳተፍ ላይ ካሉት ነዋሪዎች መካከል በዞኑ ሊበን ወረዳ የድቤ ጉቼ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲ ኑር እንዳሉት በግላቸው የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ ላይ ናቸው፡፡
የድርቅ ተጋላጭነትን በዘላቂ ልማት ለመከላከል የተጀመሩት ጥረቶች ጥሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ችግኝ መትከል ብቻውን ለውጤት እንደማያበቃም ተናግረዋል፡፡
"ልማቱ ለውጤት እስኪበቃ መንከባከብ፣ ውሃ ማጠጣት፣ መኮትኮትና ከእንስሳት ንክኪ መጠበቅ የእለት ተእለት የስራችን አካል ሊሆን ይገባል፤ ተግባራዊም እያደረግን ነው" ብለዋል፡፡
የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ አልዪና 30 ባልደረቦቻቸው ባለፉት ዓመታት በጋራ የተከሉት ችግኝ ብዛት 500 መድረሱንና ጸድቆ በጥሩ ቁመና ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አምናም በተመሳሳይ መልኩ የተከሉትን 50 የሀበሻ ጽድና ግራቪሊያ የመሳሰሉት ችግኝ ለታሰበለት ውጤት ለማብቃት በመንከባከብ ላይ ነን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ከተተከለው ውስጥ ከ78 በመቶ በላይ ችግኝ መጽደቁን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ነው፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስቀሉ ቱሉ በዞኑ የድርቅ ተጋላጭነትን ከመከላከል ያለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው 28 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ መተከላቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ከተተከሉት ችግኞች መካከል የሀበሻ ጽድ፣ ግራቪሊያ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ኮሶ፣ ሙዝ፣ አቦጋዶ፣ ማንጎና ፓፓያ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በዞኑ በተደረገ እስካሁን 22 ሚሊዮን 5 ሺህ በላይ ችግኝ እንደጸደቀ በባለሙያዎች የመስክ ምልከታ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከልም በዞኑ የተጀመረውን የችግኝ ልማት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ ባለፈው ክረምት ለተተከሉ ችግኞች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የእንክብካቤ ስራ እየተከናወነ ነው።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት አርሶ አደሮችና የመንግስት ሰራተኞች እንዳሉት የተከሉት ችግኝ ከግብ ደርሶ የሚፈለገውን ጠቀሜታ እንዲያሳካ የጀመሩትን የእንክብካቤ ስራ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
"በመትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ልምላሜን ለነገ ትውልድ ማውረስ ይኖርብናል" ያሉት የዘመቻው ተሳታፊዎች፤ "ችግኝን ካልተንከባከብን የምንፈልገውን ውጤት ማግኘት አንችልም" ብለዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ትግስት ሃምቢሳ እንዳሉት "የዛፍ ችግኝ እንደ ህፃናት ትኩረት ይሻሉ" ይላሉ።
በመሆኑም አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ለከተማው ውበትና ለሌሎች ጠቀሜታ ማድረስ ይገባል ብለዋል።
የነቀምቴ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ከድር እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት በከተማዋ ከተተከሉት ከ 2 ሚሊዮን 180 ሺህ በላይ ችግኞች 85 በመቶው መፅደቅ ችለዋል።
በከተማዋ እና አካባቢዋ የተተከሉትን ችግኞች በሚገባ በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን አክለዋል።
በእንክብካቤው ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን በዘመቻ መልክ የመንከባከብ ስራ ከዛሬ ህዳር 11 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።