ዩኤስ ኤይድ ለኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 14 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኤስ ኤይድ ለኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 14 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ)፦የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ለኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 14 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ ዩኤስ ኤይድ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመድኃኒት አቅርቦትና ተደራሽነት ላይ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት አድንቀዋል።
በመሆኑም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከናውናቸው የመድኃኒት አቅርቦት ሥራዎች እገዛና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም ዩኤስ ኤይድ በ350 ሺህ ዶላር የ14 ተሽከርካሪዎች ግዥ ፈፅሞ አገልግሎቱ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች እንዲውሉ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቅናው ካውዛ፤ የዩኤስ ኤይድ ድጋፍ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የጤና ጣቢያዎች የሕክምና ግብአት ለማቅረብ የላቀ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይም ለእናቶችና ህፃናት መድኃኒትና አስፈላጊ ግብአቶችን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ የተሽከርካሪዎቹ ድጋፍ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው፤ ለጤናው ሴክተር የሚደረጉ መሰል ድጋፎች የሕክምና ግብአቶችንና የመድኃኒት ሥርጭቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፎች እገዛ የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል።