ቀጥታ፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በኮምቦልቻ ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አስጀመሩ

ደሴ ፤ ህዳር 11/2016 (ኢዜአ) ፦የቀደመ መረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላችንን በማስቀጠል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን በሁለንተናዊ መንገድ መደገፍ እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ገለጹ፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ ቢራሮ ክፍለ ከተማ የሚገነባውን ''የሳር መንደር'' የመኖሪያ ቤቶች የግንባታ ፕሮጀክት ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላችንን አጎልብተን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን መርዳት ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው።

በተለይም በየአካባቢው ያሉ አልሚ ባለሃብቶች በዘርፎቻቸው ከሚፈጥሯቸው የስራ ዕድሎች ባሻገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን መደገፍ እንዳለባቸው ገልፀዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ ''የሳር መንደር'' የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከማስጀመራቸውም በተጨማሪ በኮምቦልቻ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አየለ በበኩላቸው፤ መኖሪያ መንደሩ በከተማ አስተዳደሩና በህብረተሰቡ ትብብር በ40 ሚሊዮን ብር የሚገነባ ነው፡፡

ተገቢውን ግብዓት በማሟላትም ባጠረ ጊዜ ውስጥ በጥራት በመገንባት ከ500 ለሚበልጡ አቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የሚተላለፍ መሆኑን አመልክተዋል።

ለመኖሪያ ቤቱ ግንባታም 2 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ግንባታውም ባለ አንድ ወለል ህንጻ፣ ግሪንኤሪያንና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን ባካተተ መንገድ ይገነባል ብለዋል።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም