ቀጥታ፡

ዓለምአቀፍ የጥራጥሬና ቅመማቅመም ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 11/2016(ኢዜአ)፦ 12ኛው ዓለምአቀፍ የጥራጥሬና ቅመማቅመም ጉባዔ " ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ፍላጎት አስተማማኝ ምንጭ " በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ዓለምአቀፍ ጉባዔውን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁትም ታውቋል። 

በጉባዔው  ከ400 በላይ የአገር ውስጥ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብአትና ማሽነሪ አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ አገራት ዓለምአቀፍ ምርት ገዥ ኩባንያዎች  እየተሳተፋ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ በጉባዔው መክፈቻ ላይ  እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች የጥራጥሬና ቅመማቅመም ዋንኞቹ ናቸው። 

ምርቶቹን በጥራትና በብዛት በማምረት የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ  መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በዘርፋ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ምቹ የንግድ ሥራ ፖሊሲ በማውጣት ጭምር  ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ የንግድ ትስስሮች ላይ በንቃት እየተሳተፈች አዳዲስ የገበያ አማራጮችንና ዕድሎችን እያመጣች መሆኑንም አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሲሳይ አስማረ፤ ጉባዔው ላይ  ዓለምአቀፍ ገዥዎችን፣ ላኪዎችን፣ የእርሻ ምርት ግብአት አቅራቢዎችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትና የተለያዩ  አገልግሎት ሰጪዎችን  በአንድ መድረክ በማገናኘት የንግድ ትስስር ይፈጥራል ብለዋል። 

ጉባዔው የሀገር ውስጥ ላኪዎች የንግድ ግንኙነታቸውን በላቀ ሁኔታ ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የንግድ ግንኙነቶችን ለመመስረት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል። 

ዓለምአቀፍ የገበያ ዕድሎችን በማስፋት አምራችና ገዥዎችን በማገናኘት በኩል ማኅበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ጉባዔው የንግድ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ የኢትዮጵያን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም