ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጤናውን ዘርፍ የማዘመንና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 11/2016(ኢዜአ)፦ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጤናውን ዘርፍ የማዘመንና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በሙከራ ጊዜ ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችም በቅርቡ ሥራ ላይ የሚውሉ መሆኑ ታውቋል።

በዚህ ዘመን በዓለም ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁለንተናዊ አገልግሎት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገና በእጅጉ እየዘመነም መጥቷል።

የሰውን ልጅ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ቋንቋና እሳቤ በላቀ አረዳድና ግንዛቤ ዳታን መሠረት በማድረግ ለችግሮችም ፈጣን መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ነው፡፡

የሰውን ልጅ ክህሎትና እውቀት ለማሽን በማስተማር ሥራን በፍጥነትና በጥራት በማከናወን ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑም ይታወቃል።   

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዕድገት በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ጃፓንና ሌሎችም አገራት በኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በስፋት ሥራ ላይ በመዋሉ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል። 

በኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም መርቀው ሥራ ማስጀመራቸውም ይታወሳል። 

ኢንስቲትዩቱ ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ጤና እንዲሁም ለኅብረተሰብ ጥበቃና ደኅንነት አገልግሎቶች ይውላል ባሉት መሠረት በእነዚህ ዘርፎች በስፋት እየተሰራበት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ፤ በመንግሥት ዲጂታል ስትራቴጂ ተቀርፆ አካታችና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት መሠረት የሚሆን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። 

ለዘርፉ ትልቅ መሠረት የጣለ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዳታ ሴንተር ተገንብቶ እየተሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።  

በተቋሙ የተሰሩ የምርምር ውጤቶችን እስካሁን ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤  ለአገር ውስጥና ለውጭ ሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ኮንፈረንሶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡   

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የስፔሻሊቲ እና ሰብ-ስፔሻሊቲ ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ታዬ ገልጸዋል።

የዘርፉን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሙከራ ጊዜ ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችም በቅርብ ጊዜ ሥራ ላይ የሚውሉ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

የህፃናትን የቆዳ በሽታ መለየት እና ማከም፣ የጡት ካንሰርን መለየት፣ የስኳር በሸታን ዓይነት፣ የጉዳት መጠን እና የወደፊት ተፅዕኖን መተንበይ የሚያስችሉና የፍትህና የጸጥታ ሥራን የሚያግዙ ከፈጠራዎቹ መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።  

በ2022 በአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም የሚያደርገውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እውን በማድረግ ላይ መሆኑንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም