የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በሩብ ዓመቱ ከ462 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ) ፦ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት ከ462 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የመንግሥት ሰራተኞች ዲጂታል የትራንስፖርት መታወቂያ ካርድ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባም ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎትን የ2016  የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት ትልቁ ባቀረቡት ሪፖርት፤ አገልግሎቱ የመንግሥት ሰራተኞችን በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ከማጓጓዝ በተጨማሪ በገቢ ረገድ ከዕቅድ በላይ ማሳካቱን ገልጸዋል።

በዚህም ሩብ ዓመቱ ከ457 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ462 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ133 ሚሊየን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም ነው ያነሱት።

ገቢው የተገኘው ከሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎችም የገቢ ምንጮች መሆኑን ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ በ455 አውቶብሶች በ102 መስመሮች ለመንግሥት ሰራተኞች በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

ከዚህም በተጨማሪም አገልግሎቱ ከሰራተኞች በተጨማሪ ለሌሎች የከተማ ነዋሪዎች በተተመነ የትራንስፖርት ክፍያ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው ብለዋል።

የትራንሰፖርት አገልግሎቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየዘረጋ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

በሁሉም የመንግሥት ተቋማት የሚገኙ የትራንስፖርት ተጠቃሚ ሰራተኞችን ትክክለኛ ቁጥር ለመለየት በየተቋማቱ ዳግም የምዝገባ እና የማጣራት ስራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው እየጨመረ ያለውን የሰራተኛ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ምን ያህል ዝግጁ ነው ሲሉ ጠይቀዋል።

የሰራተኛውን ደህንነት የጠበቀ ትራንስፖርት ለመስጠት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምን እንደሚመስል እንዲብራራላቸውም በጥያቄያቸው አንስተዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምራት ፉፋ፤ ለሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በተሽከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠር ላይ፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ፣ የአሽከርካሪ ስነምግባርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኞችን የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀሚያ የወረቀት ካርድን ወደ ኤሌክትሮኒክ በመቀየር በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለዚህም እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ ዲጂታል ካርዶች ዝግጁ መደረጋቸውን ነው ያነሱት።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ የመንግሥት ሰራተኞች የሚበዙበትን መስመር መለየት፣ ስምሪት ማስተካከልና የአገልግሎት መጨናነቅን መቀነስ አለበት ብለዋል።

በዚህም ለሰራተኞች ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋን ዜሮ ለማድረስ በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ እየተገበረ ያለው እቅድ የሚበረታታ በመሆኑ በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እንዲሰራም ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም