ህዝቡ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በየደረጃው በተካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች አረጋግጧል

ጎንደር ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ) ፦  ህዝቡ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በየደረጃው በተካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች በቂ ግብአት በመስጠትና በተሳትፎው ማረጋገጡን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ተናገሩ፡፡ 

 ''ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ጎንደርን እንገንባ'' በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የሰላም ውይይት በጎንደር ከተማ ተካሄዷል፡፡ 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የሰላም ምክክር መድረኮቹ በከተማው አሁን የተገኘውን ሰላም በህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻል ነው፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በዋነኝነት የሰላሙ ባለቤት ሆኖ እንዲንቀሳቀስ በከተማው የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ህዝቡ የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በአጽንኦት ማንሳቱን ጠቅሰው፤ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው የሚፈቱ ናቸው ብለዋል።

ከመድረኮቹ የተገኙት ግብዓቶች በከተማው የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉና አዳዲስ ፕሮጀክቶችም እንዲሰሩ ትልቅ አቅም የሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን የተገኘውን ሰላም ወደ ዘላቂነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ሃሳቦች የተነሱበትና የጋራ መግባባት የተደረሰበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡


 

የስብሰባው ተሳታፊ ወይዘሮ ሰናይት ወልደስላሴ በበኩላቸው፤ ''ስለ ከተማው ሰላም ህዝቡና መንግስት በጋራ ምን ማድረግ አለብን በሚል የጋራ ምክክር አድርገናል'' ብለዋል፡፡

በመድረኩ በገጠሙ የሰላም ችግሮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ ለሰላም ትልቅ ዋጋ መክፈል እንዳለብንም የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

''ያለ ሰላም መኖርም ሆነ መስራት አይቻልም፤ በሰላም ገብቶ መውጣትም አዳጋች ነው'' ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሪት ኮኪት ደሴ ናት፡፡

በመሆኑም በከተማው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በምንችለው መንገድ ሁሉ አጥብቀን እንሰራለን ብላለች።

በከተማው በተዘጋጁት 95 ህዝባዊ መድረኮች ላይም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም