የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ለንደን ጋትዊክ አዲስ በረራ ጀመረ

 

አዲስ አበበ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ እንግሊዝ ለንደን ጋትዊክ አዲስ በረራ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ አየር መንገዱ በያዘው የእድገት መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን እያሰፋ ይገኛል።

ዛሬ ወደ ለንደን ጋትዊክ የተጀመረው አዲስ በረራም በእንግሊዝ ከለንደን ሂትሮ እና ከማንችስተር ቀጥሎ ሶስተኛ መዳረሻው መሆኑን ገልጸዋል።

በረራው በሳምንት ሶስት ጊዜ የሚኖር ሲሆን ጋትዊክ በአውሮፓ የአየር መንገዱ 20ኛው መዳረሻ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ በረራ ለአየር መንገዱ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፥ የበረራው መጀመር ኢትዮጵያና ኢንግሊዝ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በፍጥነት እያሳደገ ሲሆን፥ በዛሬው እለት ይፋ የሆነው የእንግሊዝ ጋትዊክ የቀጥታ በረራ 136ተኛው ዓለም ዓቀፍ መዳረሻው መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም