የስራና ክህሎት ሚኒስቴር "የማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ለስራ ባህል እድገት እና ምርታማነት" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

63

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ) ፦ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር "የማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ለስራ ባህል እድገት እና ምርታማነት" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ለ 3 ቀናት ሲያካሂደው የነበረው የ2016 የመጀመሪያ ሩብ  በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተጠናቋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈርያት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ድህነትን አጥፍቶ ብልጽግናን ማስፈን ነው።

ሀገር ለመለወጥ በርካታ እድሎችና ፀጋዎች መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ይህንንም ለማሳካት የህዝብ ባለቤትነት እና አጋዥነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም በኢትዮጵያ በስራ ባህል ዙሪያ የተለያዩ የአመለካከት ማነቆዎችን የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገር ያላትን ጸጋና አቅም በኃላፊነት እና በተነሳሽነት ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ አዲስ የሥራ ባህል በማህበረሰቡ ውስጥ ለመገንባት ያለመ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ቀጣዩ የርብርብ ማእከል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በፕሮግራም ደረጃ  እንደሚመራ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን የሚያስተባብሩ አካላትን ከሁሉም የፌደራል መንግሥትና የክልል መዋቅሮች የመመልመል ተግባር እንደሚከናወን አንስተው፤ ሂደቱ በጥንቃቄ እንዲከናወን አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም