በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብዝሃነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ

ሶዶ፣ ህዳር 10/ 2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብዝሃነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዙሪያ ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ ዛሬ  ውይይት አካሄደዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ክልሉ ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩበትና ብዝህነትን ባረጋገጠ መልኩ እየተዋቀረ ነው።

በክልሉ ከ32 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚኖሩበት ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ ሁሉንም ያማከለ የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

"ክልሉ የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ የባህል፣ የሐይማኖትና ሌሎች ብዝኃነትን የሚያንጸባርቁ እሴቶች በማረጋገጥ አርአያ  እንዲሆንም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቅርቡ በወላይታ ሶዶ የሚካሄደውን የክልሉ መንግሥት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል። ውይይቱም የዚሁ እንቅሰቃሴ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ፣ የክልሉ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የክልሉን ባህል፣ ትውፊቶችና የተፈጥሮ ፀጋዎች በማስተዋወቅ ለኢንቨስትመንት የሚያመች መደላድል ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። 


 

በተለይም በመርሐ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ ስኬታማና ሰላማዊ እንዲሆን ከሃይማኖት ተቋማት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ዞን ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ሚልኪያስ ኦሎሎ ናቸው። 

ከባለሀብቶች መካከል አቶ ጥላሁን ፋንታ፣ ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች  እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

''መርሐ ግብሩ ክልሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ አብሮነታችንን የምናሳይበት አጋጣሚ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም