የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔዎችን አሳለፈ

203

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የ3ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የአስተዳደሩ አስፈፃሚ አካል በ2015 ዓመታዊ የስራ ግምገማ ወቅት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሪፎርም መደረግ ያለባቸውን ተቋማት እና አደረጃጀቶች ለይቶ የማሻሻያ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።

በዚህም ካቢኔው በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ውሳኔውን አሳልፏል፦

በማዕከል ደረጃ የሚታየውን የሠራተኛ ክምችት ቁጥር ከተማዋ ከምታመነጨው ገቢ እና ለህብረተሰብ ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር የማይመጣጠን በመሆኑ ፤ ሰራተኛውን ከፍተኛ የሥራ ጫና ወደ አለባቸው ወረዳ እና ተቋማት ስርጭት እንዲደረግ እና ይህንንም ተቋማት ሙያዊ እና ተፈላጊ ችሎታን ታሳቢ አድርገው እንዲያስተገብሩ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላልፏል።

 

በመንግስት ከሚሰራው ለ3ኛ ወገን ወጪ አውት ሶርስ ተደርገው ቢሰሩ ጥሩ እና ተፈላጊውን ውጤት ያመጣሉ ተብለው በጥናት በተለዩት አገልግሎቶች በ3ኛ ወገን እንዲሰሩ እና ሂደቱን በተመለከተ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ወደ ሰራ እንዲገቡ ተወስኗል።

የአስተዳደር ችግር እንዳያጋጥም የሽግግር ሂደት እቅድ ተዘጋጅቶ በጠንካራ የሥራ ዲሲፕሊን እንዲመራም መወሰኑም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አመልክተዋል።

በተቋቋመው የሙያተኞች ኮሚቴ ጥናት ተደርጎባቸው ተመልሰው ሪፎርም እንዲደረጉ እና በአዲስ መልክ እንዲደራጁ የተደረጉ ተቋማት ጥናት፣ የአሰራር ሂደት እና አደረጃጀት ሁኔታ ቀርቦ ውይይት መደረጉም ተጠቅሷል።

የቀረቡትን ማሻሻያ ሀሳቦች በማየት እና በመመርመር ለምክር ቤት እንዲቀርብ መወሰኑም ተመልክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም