በአፍሪካ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል--አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ) ፦ በአፍሪካ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ የቋሚ ኮሚቴዎች የጋራ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በስብሰባው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፤ አህጉሪቷ የሰው ዘር መገኛና የቀደምት ስልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኗን አንስተዋል።

አፍሪካ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም ህዝቦቿ አሁንም በሰላም እጦትና በድህነት እየተፈተኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ቀደምት አፍሪካውያን ለአህጉሪቱ አንድነትና ነጻነት በመታገል፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመመስረት ጀምሮ ለአፍሪካ ልማትና ብልጽግና ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውንም ነው ያስታወሱት።

ጠንካራ አህጉራዊ አንድነትና ብልፅግና እንዳይረጋገጥ ኢ-ሕገ መንግስታዊ የሆኑ የመንግስት ለውጦችና ስደት እንቅፋት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል አገራት ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ጠቁመዋል።

በተለይም ወጣቶች በህገወጥ መንገድ የሚያደርጉት ስደት አፍሪካ አምራች ኃይሏን እንድታጣና ልማቷ ወደ ኋላ እንዲቀር እያደረገ  መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ወጣቶች ለአህጉራቸው ዕድገት የሚተጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር እንደሚገባ አንስተዋል።

አፈ ጉባኤው አክለውም ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል የሚል ፅኑ አቋም አላት፤ ለስኬቱም በተግባር እየሰራች ነው ብለዋል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላት በአህጉሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህግ የበላይነት እንዲከበር በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ሁመድ በበኩላቸው፤ ኢ-ህገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ በአፍሪካ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዳይኖር እያደረገ ነው ብለዋል።


 

ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላት በአህጉሪቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ምክትል አፈ-ጉባኤዋ አክለዋል። 

የፓን አፍሪካ ፓርላማ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች አህጉሪቷን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ፓርላማው በአፍሪካ በተለያዩ አገራት ላይ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እገዛ እያደረገ መሆኑን በማንሳት።

ከተለያዩ የዓለም የፓርላማ አደረጃጀቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ 11 የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ያሉት ሲሆን የቋሚ ኮሚቴዎቹ የጋራ ስብሰባ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም