በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የኮሌራ በሽታን ለማከም የሚያግዙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ   

81

ሰቆጣ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የኮሌራ በሽታን ለማከም የሚያግዙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ። 

ድጋፉን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሲሆን ድጋፉም ድንኳን፣ አልጋ፣ የንፅህና መጠበቂያና ሌሎች ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

በዩኒሴፍ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ የቴክኒክ አማካሪ አቶ መላሹ ጌታነህ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በዞኑ የኮሌራ በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን ስራ እያገዘ ይገኛል።

በዛሬው እለትም ለ5 ወረዳዎች የሚያገለግል 11 አይነት የኮሌራ በሽታ ለማከም የሚያገለግል ቁሳቁሶች ድጋፍ ማደረጉን ተናግረዋል። 

ድጋፉም 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኮሌራ በሽታ ታካሚዎች የተሻለ ህክምና መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ በበኩላቸው ድጋፉ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎችን በተሟላ መንገድ ለማከም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበው፤ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች በህክምና ተቋማት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም