በአማራና አፋር ክልሎች  የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መተግበር ከጀመረ ወዲህ በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

80

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦  በአማራና አፋር ክልሎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መተግበር ከጀመረ ወዲህ በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሎቹ ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በአገሪቱ ያለውን የጤና ፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት በመንግሥት ይፋ የተደረገ ፕሮግራም ነው።

ፕሮግራሙ  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 690/2002 የፀደቀ ሲሆን፤ ደመወዝተኛ ያልሆነውንና መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ ነው። 

እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በሙከራ ደረጃ የነበረው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በ2009 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ ሙሉ ትግበራ ተሸጋግሯል።

ኢዜአ ፕሮግራሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች በጤናው ዘርፍ ያመጣውን ለውጥ አስመልክቶ ከጤና ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለዘላቂ የጤና ልማት ግንባታ ጠንካራ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ጠንካራ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር ደግሞ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት በተለይ በአማራ ክልል በፕሮግራሙ መታቀፍ ከሚገባው የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ 96 በመቶው የሚሆነውን አባል ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ በተከናወነው ተግባርም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር  መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

አሁን ላይ ሕብረተሰቡ በጤና ተቋማት የመገልገል ምጣኔው 1 ነጥብ 8 መድረሱን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህም በክልሉ በገንዘብ እጦት ሕክምና ማግኘት የማይችሉ ዜጎች ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መተግበር ከጀመረ ወዲህ በጤናው ዘርፍ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመላክተዋል፡፡


 

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢ በበኩላቸው፤ በክልሉ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የሕክምና ወጪ ተግዳሮትን ለመቋቋም አዋጭነቱ በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በሦስት ወረዳዎች ብቻ ይተገበር የነበረው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አሁን ላይ ወደ 15 ወረዳዎች ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ አባል የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህም ሕብረተሰቡ በጤና እክል ወቅት ይገጥመው የነበረውን የገንዘብ እጥረት መቀነስ አስችሏል ብለዋል፡፡

ኃላፊዎቹ በክልሎቹ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም