የኢዜአ አመራርና ሰራተኞች ለ13ኛ ጊዜ ደም ለገሱ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አመራርና ሰራተኞች ለ13ኛ ጊዜ ደም ለገሱ።

የተቋሙ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ሙያዊ ግዴታቸውን ከመወጣት ባለፈ በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ።

በተለይም በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በተደጋጋሚ የሚሳተፉ ሲሆን በዛሬው እለትም ለ13ኛ ጊዜ የደም ልገሳ አድርገዋል።

ከደም ለጋሾቹ መካከል የኢዜአ የሚዲያ እቅድና ስትራቴጂክ ስራ አመራር ዳይሬክተር ብርቅነሽ ዘርፉ፤ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተሩ ዮሃንስ ወንድራድ እና የዜና ማእከል ባለሙያዋ የንጉስ ውቤ፤ ደማቸውን ለወገኖቻቸው በመለገሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።  


 

ከወሊድ ጋር በተያያዘ በደም እጥረት ህይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቁ እናቶችንና በአደጋ ምክንያት ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ሁላችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።

የእናቶችና ህፃናትን ህይወት መታደግ ከምንም በላይ የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በቀጣይነት የመለገስ እቅድ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

የደም ልገሳን ባህል በማድረግ ሁላችንም ሰብአዊነትን ማስቀደምና የወገን አለኝታነታችንን በተግባር ማረጋገጥ አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 


 

በኢዜአ የሴቶች እና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ  የተቋሙ ሰራተኞች በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ መርሃ ግብርን ባህል አድርገው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ለ13ኛ ጊዜ ደማቸውን መለገሳቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ደም ለሚሹ ወገኖች ደም በመለገስ የዜጎችን ህይወት መታደግ የሁላችንም መልካም ፈቃድና ባህል ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም