የሕብረት ሥራ ማኅበራት ሚናቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያግዝ የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕብረት ሥራ ማኅበራት ሚናቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያግዝ የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ)፦የሕብረት ሥራ ማኅበራት ገበያውን የመምራት ሚናቸውን በብቃት ለመወጣትና አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ በኑሮ ውድነት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንዳይጎዱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ለሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብና በእሁድ ገበያ ምርቶችን በማቅረብ ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ አርሶ አደሮች ቀጥታ ምርቶቻቸውን መሸጥ እንዲችሉ ለማስቻል የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል የሕብረት ሥራ ማኅበራትን አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመንና የመዋዕለ-ንዋይ አቅማቸውንም ማሳደግ ትልቅ እገዛ እንዳለውም ይገለጻል።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሕብረት ሥራ ማኅበራት በተለይ በግብርናው ዘርፍ ሚናቸውን ሲወጡ ቢቆዩም ከማስፈጸም አቅም ጋር በተያያዘ ችግር ይስተዋልባቸዋል።
98 በመቶ ማዳበሪያ ሥርጭት እንዲሁም 35 በመቶ ምርጥ ዘር በሕብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ሲከፋፈል መቆየቱንና፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በኪራይ ሲያቀርቡ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ሕብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶአደሩ የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ባዛርና ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የግብርና ምርቶችን ለአዲስ አበባ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
ሆኖም በቁጥራቸው ልክ ገበያው ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ባለመሆኑ ያለባቸውን የአደረጃጀትና የአሠራር እንዲሁም የአቅም ችግር ለመፍታት የሚያስችል ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ ሕብረት ሥራ ማኅበራቱ ሰፊ ተግባር ቢያከናውኑም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ዋጋ አውጥተው የመግዛት አቅም እንዳልገነቡ ነው የሚናገሩት።
በተለይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ዋጋውን በተዘዋዋሪ በማውጣት የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ እያባባሱት መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ የሚተገበረው ሪፎርም ይህንን ችግር እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል።
በሪፎርሙም በተያዘው ዓመት በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች ከግብርና ሚኒስቴርና ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በሁሉም ክልሎች ያሉ ሕብረት ሥራ ማኅበራት በእሁድ ገበያ ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ሸማቹ ከደላላ ጣልቃገብነት ውጭ ምርቶችን ከአምራቾች እንዲገበይ ለማስቻል የተጠናከረ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።