በሶማሌ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ከ19 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማድረስ ተችሏል- የክልሉ ውሃ ቢሮ

77

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2016(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ከ19 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የክልሉ ውሃ ቢሮ  አስታወቀ።

የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጿል።

በጅግጅጋ ከተማ የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዝግጅትና የክልሉን አጠቃላይ ልማት እየጎበኙ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች ዛሬ የጅግጅጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተሰሩ የልማት ሥራዎችን  ተመልክተዋል። 

በሶማሌ ክልል ውሃ ቢሮ የመጠጥ ውሃ የሥራ ሂደት ኃላፊ አብዲ ከድር ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፤ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ የክልሉን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት ሰፋፊ ተግባራት ተከናውነዋል። 

የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል በከተማ 29፥ በገጠር ደግሞ 13 የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን አንስተዋል። 

በዚህም የገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከለውጡ በፊት ከነበረበት 18 ከመቶ አሁን ላይ ወደ 41 ነጥብ 5 ከመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በከተሞች ደግሞ 20 ከመቶ የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ወደ 47 ነጥብ 88 ከመቶ በማሻሻል አጠቃላይ የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ19 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል። 

የጅግጅጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ ከከተማዋ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ከምትገኘው ፋፈን አካባቢ 8 ጥልቅ ጉድጓድ በመቆፈር ወደ ስራ መግባቱንም ነው የጠቀሱት።

በዚህም  ከተማዋ በቀን ታገኝ የነበረውን የውሃ መጠን በእጥፍ በማሳደግ በአሁኑ ወቅት 20 ሺህ ሜትር ኪዮቢክ እንድታገኝ መደረጉን አስረድተዋል።

በዚሀም የጅግጅጋ ከተማ የውሃ አቅርቦት ሽፋን ወደ 50 መቶ  ከፍ ማለቱን ነው ያብራሩት።

የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁንም ብዙ መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሉ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የጅግጅጋ ከተማ የምዕራፍ ሁለት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር በድሪ አሊ ሁሴን በበኩላቸው፥ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን እድገትና ስፋት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተገነባው ምዕራፍ ሁለት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም ከከተማዋ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት በጥልቅ የከርሰ ምድር ጉድጓድ ቁፋሮ ውሃ በማውጣት የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ከኅዳር 25 እስከ 29/2016 ዓ.ም ድረስ በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ ከተማ በድምቀት ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም