ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሁለቱ አገራት ግንኙነትን በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከ"ጂ-20 ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ አስቀድሞ ከጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች በጋራ ትብብር መስኮች፣ በአገር ውስጥና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

ውይይቱን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የቆየና ጠንካራ መሆኑን ገልፀዋል።

የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ለማጠናከር እንዲሁም አገሪቱ የምግብ ዋስትና እንድታረጋግጥ ትብብር እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር ይህንን ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። 

ይህንንም ተከትሎ በተለይም የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት የኢንቨስትመንትና የልማት ትብብር ለማድረግ መወያየታቸውንም ተናግረዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በግብርናው ዘርፍም ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም የባለብዙ ወገን ዘርፍ አጋርነትን ለማጎልበት ሁለቱ መሪዎች መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም