ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የትብብር ግንኙነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የትብብር ግንኙነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የኢትዮጵያና የጀርመንን የትብብር ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር ያደረጉትን ምክክር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በአካባቢና አለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ተናግረዋል።
መሪዎቹ የኢትዮጵያና ጀርመን ሚዛኑን የጠበቀ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ነው አምባሳደር ታዬ የገለጹት።
በምክክሩ ጀርመን በኢትዮጵያ የምትሰማራባቸው ልዩ ልዩ የኢንቨስተመንት አማራጮችን በጋራ ለመለየት ተችሏል ብለዋል።
የጀርመን ተቋማት በኢትዮጵያ በኢነርጂና በአፈር ማዳበሪያ ዘርፎች መሰማራት በሚችሉበት ጉዳዮች ዙርያም ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን ነው የተናገሩት።
ከምጣኔ ሀብት እድገት ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እዳን በማቃለል እና ማሸጋሸግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም መምከራቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውስጥ ችግር ለመፍታት መንግስት ያከናወናቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን ያስታወቁት አምባሳደሩ በአሁኑ ወቅትም ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት እንደ ሀገር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣናው እና በሱዳን ያለውን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ያከናወነችውን ተግባርና እየተጫወተች የሚገኘውን ገንቢ ሚና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማስታወቃቸውን አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አስረድተዋል።