የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 10/2016 (ኢዜአ) ፦ አምስተኛው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ጉባኤ በኢትዮጵያ ተባባሪ አዘጋጅነት ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው “ቀጣይነት ያለው የመሬት አስተዳደር ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ፈጣን ትግበራ” በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

ጉባኤውን የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ማዕከል፣ የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት በተባባሪነት እንዳዘጋጁት ተመልክቷል።

የአፍሪካ ሀገራትን የመሬት ፖሊሲ ትግበራን በመረጃ፣ ክህሎትና እውቀት ማሳደግ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ መምከር የጉባኤው አላማ እንደሆነም የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።

ተግባራዊ የተደረጉ የመሬት ፖሊሲ ልምዶችን በመጠቀም ትስስርን መፍጠርና ልምድ መለዋወጥ እንዲሁም የአህጉሪቱን የመሬት ፖሊሲ አቅም ማሳደግም የጉባኤው ሌላኛው አላማ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም