በዶሚኒካን ሪፐብሊክ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
በዶሚኒካን ሪፐብሊክ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 21 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

አዲስ አበባ ፤ህዳር 10/2016(ኢዜአ)- በዶሚኒካን ሪፐብሊክ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ህጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ሁነኛ መፍትሔ ባልተገኘለት የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች እየተከሰቱ ይገኛል።
ካሪቢያዊቷ ዶሚኒካን ሪፐብሊክም ባለፉት 48 ሰዓታት ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው እጅግ ከፍተኛ ዝናብ መጠነ ሰፊ ጉዳት አስተናግዳለች።
ፍራንስ 24 የሀገሪቱን ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ዋና ከተማዋ ሳንቶ ዶሚኒጎን እና ሌሎች አካባቢዎችን ባካለለው አደጋ መኖሪያ ቤቶችና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።
አደጋው በሰዎች ላይ ባስከተለው ጉዳትም በጉዞ ላይ የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላትና 3 ህጻናትን ጨምሮ እስካሁን 21 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በአንዳንድ አካባቢዎችም የኤሌክትሪክና ሌሎች አገልግሎቶች የተቋረጠ ሲሆን በሚቀጠሉት 24 ሰዓታት የአደጋው ሁኔታ ሊከፋ እንደሚችል ተመልክቷል።
በዚህም 13 ሺህ ገደማ ሰዎችን የአደጋ ቀጠና ተብለው ከተለዩ 32 አካባቢዎች ማንቀሳቀሱን የሀገሪቱ የድንገተኛ አገልግሎት ማእከል ገልጿል።
ፕሬዚዳንት ልዊስ አቢናዳር ክስተቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ “የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ችግር ቸል ያሉ በጉዳቱ ሀገራችን ምስክር ናት፤ በታሪክ እጅግ ከፍተኛ ዝናብ አስተናግደናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ትምህርት ቤቶች ለተወሰኑ ቀናት አገልግሎት እንደማይሰጡ ጠቁመው የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።