የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የብዝሃነት አያያዝና አስተዳደር እንዲዳብር አስተዋጽኦው የጎላ ነው-አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የብዝሃነት አያያዝና አስተዳደር እንዲዳብር አስተዋጽኦው የጎላ ነው-አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
ባህር ዳር ፤ ህዳር 9/2016(ኢዜአ)፦ “የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የብዝሃነት አያያዝና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እንዲዳብር አስተዋጽኦ እያደረገ መጥቷል” ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ ሦስተኛ ዙር ሰልጣኞች 18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዛሬ አክብረዋል።
አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የህዝቦች ምንነት እንዲከበርና ለዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት መሰረት የጣለ ነው።
በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ ውበትን የጋራ ሃብት በማድረግ አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችልና የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ደረጃ የተደረገው የመክፈቻ ፕሮግራም ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የመንግስት አመራር አባላት በተገኙበት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከህዳር 1 ቀን ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በመከበር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስት ግንኙነት ፣የዴሞክራሲ ግንባታና የህገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንች ይርጋ መለሰ ናቸው።
ቀኑ ”ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ አገራዊ አንድነትንና ኢትዮጵያዊ ብዝሃነትን በሚያንጸባርቁ ሃሳቦችና መልእክቶች እየተከበረ መሆኑን ገልፀዋል።
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ኢትዮጵያ ብዝሃነት ያለባት ሀገር መሆኗን እውቅና ከመስጠት ባለፈ ወቅቱ ከመቼውም በላቀ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የግድ የሚልበትና የጋራ ጉዳዮችን በጋራ መፍታት የሚቻልበት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
የማጠቃለያ ፕሮግራሙ በሱማሌ ክልል አዘጋጅነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በጅግጅጋ ከተማ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያ ወደ ምትጠበቅበት ክብሯና ከፍታዋን የሚያሳይ ነው ያሉት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ አቶ መለሰ አለሙ ናቸው።
እንዲሁም ሀገሪቷ የብዝሃነት ሀገር መሆኗን ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በየደረጃው እየተሰጠ ያለው የመንግስት አመራር አባላት ስልጠናም ይህንን እውን ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ ማምሻውን በተከበረው በዓል በባህር ዳር ማዕከል በሦስተኛ ዙር ስልጠና እየተሳተፉ የሚገኙ አመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።