የኩባ ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያ መሥዋዕትነት ለከፈሉ የኩባ ወታደሮች የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ - ኢዜአ አማርኛ
የኩባ ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያ መሥዋዕትነት ለከፈሉ የኩባ ወታደሮች የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኩባ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር ቫልዴስ ሜሳ ለኢትዮጵያ በመወገን መሥዋዕትነት ለከፈሉ የኩባ ወታደሮች በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም የኢትዮጵያ እና የኩባ ወዳጅነት ዘመናትን የተሻገረና የደም ቁርኝት ያለው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን በርካታ ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት አይነቶች በማስተማርም ኩባ ባለውለታ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የኩባ ወታደሮች በኢትዮጵያ የህይወት መስዋእትነት የከፈሉት በ1969 ዓ.ም በወቅቱ በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ መንግስት ወረራ መፈጸሙን ተከትሉ በነበረው ውጊያ መሆኑ ይታወሳል።
በወቅቱ ኩባ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ያደረገች ሲሆን መስዋእትነት ለከፈሉ ወታደሮቿ በአዲስ አበባ ኩባ ፓርክ የመታሰቢያ ሃውልት ቆሞላቸዋል።
ምክትል ፕሬዚደንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስከበር ሲዋጉ ለተሰው የኩባ ወታደሮች መታሰቢያነት የቆመ መሆኑ ይታወቃል።