የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመልስ ጨዋታ የማሊ አቻውን 4 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸነፈ

147

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመልስ ጨዋታ የማሊ አቻውን 4 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ጨዋታውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ጅራ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ባህሩ ጥላሁንና የፊፋ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ተከታትለውታል።

እ.አ.አ በ2024 በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 11ኛው የፊፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት በተደረገው ጨዋታ ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ በ35ኛውና በ45ኛው ደቂቃ በእሙሽ ዳንኤል አማካኝነት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች እየመራ ለእረፍት ወቷል።

ከእረፍት መልስ ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴት ብሔራዊ ቡድን መዓድን ሳህሉ በ66ኛው ደቂቃ እንዲሁም መሳይ ተመስገን በ69ኛው ደቂቃ ጎሎችን አስቆጥረው ቡድኑ 4 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ቡድኑ ባሳለፍነው ቅዳሜ ኅዳር 1/2016 ባማኮ ላይ ባደረገው ጨዋታ ንግስት በቀለ በ57ኛው ደቂቃ እና እሙሽ ዳንኤል በ68ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።


 

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ የማሊ ብሄራዊ ቡድንን በድምር ውጤት 6 ለ 0 አሸንፏል።

በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 16 አገራት የሚካፈሉ ሲሆን ከኮሎምቢያ ውጪ ያሉትን ቀሪ 15 ተሳታፊ አገራት ለመለየት በስድስት አህጉራት የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት አገራት የማሳተፍ ኮታ እንዳላት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) አስታውቋል።

በውድድሩ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ 35 የአፍሪካ አገራት እየተሳተፉ ነው።

የፊፋ ከ20 ዓመት የሴቶች ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ በአራት ዙሮች እንደሚከናወን የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጨረሻው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዙር ሞሮኮን እንደሚገጥም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም