በባህር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - የስልጠና ተሳታፊ አመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - የስልጠና ተሳታፊ አመራር አባላት
ባህር ዳር፤ ህዳር 9/2016(ኢዜአ)- በባህር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኢንዱስትሪና የመሰረተ ልማት ስራዎች የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ የሦስተኛው ዙር ስልጠና ተሳታፊ የመንግስት አመራር አባላት ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ባለው ስልጠና እየተሳተፉ የሚገኙ የመንግስት አመራር አባላት በከተማዋ የሚገኙ የኢንዱስትሪና መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ጎብኝተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ትእግስት ዓለሙ እንደገለጹት፤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች የህዝብ ጥያቄ የሚመልሱና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።
በተለይም 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር ስፋት ያለው አዲሱ የዓባይ ድልድይ እንዲሁም የእንስሳት መኖና የዘይት ማምረቻ ፋብሪካዎች "የከተማዋ የእድገት ደረጃ እየተፋጠነ መሆኑን ማሳያ ናቸው" ብለዋል።
''የባህር ዳር ከተማ ጽዳት፣ ውበትና መዘመን ለሌሎች የአገራችን ከተሞች ምሳሌ የሚያደርጋት ነው'' ያሉት ደግሞ ሰልጣኝ ከድር ሙሐመድ ናቸው።
የጎበኙት የእንስሳት መኖ ፋብሪካም የእንስሳት መኖን በስፋት በመላ አገራችን በማቅረብ በዶሮና እንስሳት ተዋጽኦ የሚስተዋለውን የምርት እጥረት ለማቃለል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አሁን ላይ በወተት፣ እንቁላል፣ ስጋና ሌሎች ተዋጽኦዎች የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት በመግታት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ እንዲቀርብ የሚያስችል መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
በስልጠናው እና በጉብኝቱ ያገኙት እውቀትና የጎበኟቸው ፕሮጀክቶች ለቀጣይ ስራቸው ግብአት ያገኙበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ጀረል ሙሳ ናቸው።
በተለይም አዲሱን የዓባይ ድልድይ ሲጎበኙ ዓባይ የሚመነጭበትን አካባቢ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር አስተሳስሮ በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይሄን ሀብትና ጸጋ በአግባቡ መጠበቅና ማልማት ከተቻለ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እድገትን ከማረጋገጥ ወደ ኋላ የሚመልሰው ሃይል እንደማይኖር መገንዘብ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፤ በከተማዋ በርካታ የመሰረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ማምረት የጀመሩትን 333 ጨምሮ ባጠቃላይ ከ800 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ የሚገኙ ሲሆን፤ ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም ሰልጣኝ አመራር አባላት የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የዘይት ፋብሪካዎችን፣ የአረንጓዴ ልማት ስፍራዎችንና አዲሱን የዓባይ ድልድይ በማስጎብኘት የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት መሰራቱን ገልፀዋል።
በባህር ዳር ከተማ በሚሰጠው የሦስተኛው ዙር ስልጠና ከ1 ሺህ 400 በላይ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የአመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።