በድሬዳዋ በስፖርት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ መሠረተ ልማቶች ድሬዳዋ በእግርኳስ የነበራትን ዝና ለመመለስ ያስችላሉ--ተጫዋቾችና አሰልጣኞች 

ድሬዳዋ፣ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ)---የድሬዳዋ አስተዳደር የስፖርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ የሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ከተማዋ በእግርኳስ የነበራትን ዝና ለመመለስና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዙ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ተናገሩ።

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዋና ፀሐፊ  ፋትማ ሳሙራ በዚህ ሣምንት በከተማዋ የሥራ ጉብኝት ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።



የባለሥልጣኗ ጉብኝት በተተኪ ወጣት ስፖርተኞች ውስጥ መነቃቃት መፍጠሩን በድሬዳዋ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርት ማህበረሰብ አባላት ገልጸዋል ።

የድሬዳዋ ዋልያ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ኤልያስ ሚካኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ የስፖርት ሁለገብ ማዕከልና የመጫወቻ ሜዳዎች በቀጣይ ተተኪና ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞች ለማፍራት ያግዛሉ።

በተለይ የፊፋ ዋና ፀሐፊ በድሬዳዋ ተገኝተው በከተማዋ በእግር ኳስ ስፖርቱ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች መመልከታቸው አስደሳች እና መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን ነው የገለፁት።

 



የአዲስ ከተማ ክለብ ተጫዋች ያሬድ ጌታቸው በበኩሉ ድሬዳዋ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥና ዝነኛ ተጫዋቾች በማፍራትና ከተማዋን በትላልቅ የአፍሪካ ጨዋታዎች ያስጠሩ ባለ ተስጥኦ ተጫዋቾች መፍለቂያ እንደነበረች አስታውሷል ።


ይህንን ዝና ለመመለስ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና ካቢኔ ለስፖርት ዘርፍ የሰጡት ትኩረት አስደሳች መሆኑን ተናግሮ "ተተኪና ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ለማፍራት የሚደረገው ጥረት በውጤት እንዲታጀብ ለአሸዋ ሜዳዎችና ተጫዋቾች ትኩረት መስጠት ይገባል"  ብሏል።


''የድሬዳዋ ከተማ አሁንም የምርጥ ተጫዋቾች መፍለቂያነቷ አልነጠፈም፤ ምርጥና ተተኪ ተጫዋቾች የማፍራቱ ሂደት አስደሳች ነው።'' ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ሥር የተዋቀረውን የድሬዳዋ ተተኪ ስፖርተኞች ቡድን የሚያሰለጥኑት ኢንስትራክተር አካዳሚ ከበደ  ናቸው።


 


ኢንስትራክተር አካዳሚ እንደሚሉት እሳቸው ከሚያሰልጥኗቸው አዳጊ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለብሔራዊ ቡድን ወጣቶች ቡድን ተመርጦ መጫወት  ጀምሯል።


ሰልጣኞቹ በፊፋ ዋና ፀሐፊ መጎብኘታቸውና መበረታታቸው በልጆቹም ሆነ በአሰልጣኞቹ ውስጥ ተስፋና መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል።


በተቀናጀ መንገድ ተጋግዞ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ  እንደሚያስፈልግም  ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በጉብኝቱ ላይ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ፊፋ ያስቀመጣቸውን  የጥራት ደረጃዎች የሚያሟላ አንድም ስታዲየም ባለመኖሩ ብሔራዊ ቡድኑ በራሱ ሜዳ መጫወት የሚገባቸውን ጨዋታዎች በሌሎች አገሮች ለማጫወት ተገዷል።


በድሬዳዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ እየተጠናቀቁ ያሉት የመሠረተ ልማት ሥራዎች ብሔራዊ ቡድኑን ከስደት ወደ ቤቱ እንደሚመልስ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም